እርሱ ዳግም በበረት ተወልዷል!

እርሱ ዳግም በበረት ተወልዷል!

በጎችን ለመጠበቅ ውጪ ያደሩ ምስኪን እረኞች፣ የእንግዶች ማረፊያ ስፍራ አለመኖር እና የከብቶች በረት፣ የእግዚአብሔር መላዕክት እና ሰብዓ ሰገል፡፡ እነዚህ በሁለቱ ወንጌላት ላይ ተሰባጥረው የተቀመጡ ትርክቶች ለረጅም አመታት፤ ይህ ወቅት በደረሰ ቁጥር የምሰማቸው እና የማነባቸው ቢሆኑም ዘወትር የማይሰለቹኝ ሚስጥራትን የተሸከሙ ትዕይንቶች የተከታተሉባቸው ገቢራት ሆነው ይታዩኛል፡፡ አለማት ሁሉ የተፈጠሩበት “ቃል” እነሆ ስጋ ሆነ! ነገር ግን ከተመልካች ሁሉ እረኞችን ለምን መረጠ? ከማረፊያ ስፍራ ሁሉ ለምን በከብቶች በረት ይህን አለም ተቀላቀለ?

                    እጅግ ዝቅ ብሎ. . .

በግሪኮ-ሮም የአገዛዝ ስርዐት በባርነት ቀንበር ስር የነበረችው የይሁዳ ምድር በጀብድ ታሪክ በተሞሉት የነገስታት መዋልዕ እና የተስፋ ቃላት ባሉባቸው የዳዊት መዝሙራት፤ የእግዚአብሔር ታምራት በሰፈረበት ቶራህ ይልቁንም በሚያፅናኑ የነቢያት ቃላት ልባቸው በሚቃጠል ዜጎች የተሞላች ነበረች፡፡

እጅግ ሀያል በሆነ ክንድ ከግብፅ ምድር ነፃ  ስላወጣቸው አምላክ እየተማሩ ያደጉ ቢሆኑም፤ በእውነታው ግን የሮምን መራር አገዛዝ ተቀብለው እየኖሩ ናቸው፡፡ ይህ እውነታ በውስጣቸው የፈጠረው ምሬት ተስፋን ወልዷል- “መሲሁ በሚመጣ ጊዜ ከሮማውያን አገዛዝ ነፃ ያወጣናል” የሚል!

አምላክ ተዛመደን  የሚለውን መጣጥፍ እዚህ ያንብቡ

እናም ማንም አይሁዳዊ መሲሁን በንጉስ እልፍኝ እንጂ በበረት ሊያይ አይወድም፤ ክርስቶስን በሊቀ ካህናቱ አልያም በልዑላን ሊታጀብ እንጂ በእረኞች እንዲከበብ አይመርጥም፡፡ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ስለ አካሉ ሳይሆን ስለጥላው ሲጨነቁ የኖሩ ካህናት ሳይቀሩ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከሀጢያት ባርነት ነፃ ለማውጣት ስለመወለዱ ሳይሆን፤ ድፍን እስራኤልን ከጨቋኞች ነፃ ስለማውጣቱ ሲያስተምሩ ነው የኖሩት፡፡ ጥበቃቸው ልክ ይመስለኛል- በብሉይ ቃላቱ ስለ መሲሁ ነጻ አውጪነት ተተንብይዋል፡፡ ባለኪዳኖቹ ህዝቦች ደግሞ ከዚህ በላይ ነጻነትን የሚሹበት ወቅት የለም፡፡

እርሱ ግን እጅግ ዝቅ ብሎ፤ ራሱንም አዋርዶ ወደዚች ምድር መጣ፡፡ በተጠበቀበት ቦታ ሳይሆን- ባልታሰበበት አቅጣጫ፤ ይከቡታል ተብለው በሚታሰቡ ታዳሚዎች ፊት ሳይሆን- በእረኞች መሀል የመወለዱ ብርሀን ታየ፡፡አምላክ ሰው ሆነ! ፈጣሪ የፈጠረውን ስጋ ለበሰ፡፡ እኛን ከሀጢያት ባርነት ነፃ ሊያወጣ እርሱ በባሪያ አምሳል ተገኘ- ራሱን አዋረደ- ባዶ አደረገ፡፡ የዘመን አጋሮቹ ከምድራዊ ባርነት ያላቅቃቸው ዘንድ ሲሹት እርሱ ግን የሰው ልጅን ሁሉ ከሀጢያት ባርነት ይታደግ ዘንድ ወደምድር መጣ፡፡ እንደማንኛችንም ይህችን አለም አልቅሶ ተቀላቀለ- ሊያውም ምቾት በማይሰጥ ቦታ፡፡ እጣን እና ከርቤን በታጠኑ ክፍሎች ሳይሆን ለአፍንጫ የሚሰነፍጥ የከብቶች ፅዳጅ በሞላበት ደብዛዛ በረት! ለምን? ለምን? ይህ ሁሌም በውስጤ የሚያቃጭል ጥያቄ ነው፡፡

                 ባለቅኔው አምላክ. . .

አምላኬን እንደባለቅኔ አየዋለሁ፡፡ ወደምድር በገባበት ክስተት ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ትዝብቴ ራሱን በምሳሌ ሲያስረዳን፤ በቅኔ ሲያዜምልን አደምጠዋለሁ፡፡ ጥላ እና አካል፤ ምሳሌ እና እውነታ፤ ትርክት እና ክስተት እያደረገ ሲያሻው አስቀድሞ ይመክረናል፡- ሲፈልግ ያለንበትን ያስረዳናል፡፡ እናም በእነዚህ ቀዝቃዛ እና ረጅም የገና ሌሊቶች ለምን ክርስቶስ በዚህ መልኩ እንደተቀላቀለን ሳስብ ይህ ባለቅኔው ጌታዬ ምናልባት ሊያስረዳኝ ያሰበውን ያገኘሁት መሰለኝ፡፡

ከልቤ በላይ የማይመች በረት የቱ ነው; በሀጢያት ብዛትስ ከእኔ ልብ ይልቅ የከረፋ እና የቆሸሸ ደብዛዛ በረት ይኖር ይሆን? አይመስለኝም፡፡ ከእኔ በላይ የአለም ጥበብ የማይገባው እና እጅግ የተናቀ “እረኛስ” ወዴት አለ? አዎን! ክርስቶስ ወደምድር በበረት ቢመጣም ከሀጢያት ባርነት ሊያድን የወደደው ግን እኔን ነው፡፡ ክርስቶስ ዳግም የተወለደበት መራሩ በረት የእኔ ማንነት መሆን አለበት! ባለቅኔው እርሱ ከሞቱ በኋላ የሚወለድበትን በረት አስቀድሞ ሊነግረን ወደ አለም ዝቅ ብሎ መጣ፡፡ እናም ይህን የክፋት ስር የሆነ ብርሀን የለሽ ልቤ በ”ገናው” ተወልዶበት በ”ፋሲካው” ደግሞ ያጸዳው ይዟል፡፡ በአለም ካለ ውዳቂው ቦታዎች የመጨረሻ በሆነው ተወለደ፤ በአለም እጅግ የተናቁትን ታዳሚዎቹ አደረገ- ታዲያ ይሄ በአለም የተናቅን ከሆንነው ከእኛ እና በምድር ሁሉ ቆሻሻ ከሆነው ልባችን አይገናኝምን? መልካም የልደት በዐል!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *