“እንደቤትህ ቁጠረው”

የእንግድነት ስሜትን አትንኖ የሚያጠፋ፤ ከሰዎች ጋር ቶሎ ሊቀርቡ የሚሹ ተግባቢ ሰዎች ግብዣ-እንደቤትህ ቁጠረው፡፡ ይህን ቃል ከሰማህበት ቅፅበት አንስቶ ላይህ ላይ የተመረገው ጭንቀት ሁሉ ይጠፋል፡፡ በዝምታ የሸበበህን ቤት በሁካታ ትሞላዋለህ- በአደብ የያዘህን እልፍኝ አልፈህ ጓዳ ድረስ ትዘልቃለህ፡፡ በቤቱ ውስጥ የእኔነት ስሜትህ ያይላል፡፡ ያለ መግደርደር ትመገባለህ፤ ያሻህ ላይ ታርፋለህ፤ የወደድከውን ትመለከታለህ ቀኑ ሲያይል ደግሞ ያለፍርሀት ትሟገታለህ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ግን እንደቤትህ ቁጠረው በሚል ግብዣ እና እንግድነትን በሚያስረሳ አቀባበል የተነሳ ነው፡፡ አዎ እናም ቀስ በቀስ እዚያ የእንግድነት ቤትህ ስትገባ የነበረው የራስህን ቤት የመናፈቅ ስሜት እየደበዘዘ፤ እዚህ የመቆየት ፍላጎትህ እያየለ ትሄዳለህ- አሁን ያለህበትን እንደቤትህ ቆጠርኸው፡፡

እንደቤትህ ቁጠረው ይልሃል የዚህ አለም ገዢ፡፡ “ሳሎን እና ጓዳው፤ እልፍኝ እና ማጀቱ፤ ጓሮው እና ድንበሩ ሁሉ ያንተ ማለት ነው፡፡ ፍጹም እንግድነት እንዳይሰማህ”

ሌላው አንጻር

የደግ ሰው ግብዣ ይመስላል፡፡ በቃል ብቻ የቀረበ ሳይሆን ልክ እንደቤታችን እንቆጥረው ዘንድ ያሻን በደጃችን ቀርቧል፡፡ በ ሳቅ እና በፌሽታ፤ በስራ ስኬት እና በተድላ፤ አይደለም ቤታችንን ራሳችንን እስክንረሳ ድረስ ተከበናል፡፡ እሱ ካላሻን እና “በጨለማ የምንዝናናበት” ካሰኘን ስጋን ሊያስደስት በሚችል የምኞት አለም እንዋኝ ዘንድ ሁሉን በቅርብ እና ያለመጠን አመቻችቶልናል፡፡ እንግዳን መቀበል እና ማላመድ ያውቅበታል፡፡

እናም ቀስ በቀስ ቤታችንን ረሳን- በአለም ከቶ የማይናወጥ የሚመስል መሰረት ጣልን-ተላመድን፡፡ የቀድሞው ቤት ትዝታው እንኳን ጠፋ፡፡ ወደዚህ የተላክነው ወደብርሃን የጠራንን የእርሱን በጎነት በዚህ ላሉት እንነግር ዘንድ ነበር- ያውም “ወዳጆች ሆይ ነፍስን ከሚዋጋ ስጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶች እና መፃተኞች እንደመሆናችሁ እለምናችኋለሁ” ከሚል ተማጥኖ ጋር፡፡

እንደቤትህ አትቁጠረው ወዳጄ! ያንተ ቤት ስላልሆነ ምቾት አይሰማህ፡፡ የላከህ ጌታህ- የቤትህ አባወራ መቼ እንዲመለስ አታውቅም እና እንደርስት በተሰጠህ ምድር ላይ እንኳን ድንኳንህን ተክለህ ኑር፡፡ የዚህ አለም ሰፊ ሳሎን አልያም ምቹ እልፍኝ አይሸውዱህ- እንደቤትህ አትቁጠረው፡፡ “እንደቤትህ ቁጠረው” የሚልህም ካለ የዘላለም ቤትህን ተስፋ በጊዜያዊ ፈራሽ ድንኳን ፤ የከበረ በኩርነትህን በመናኛ ምስር ሊደልልህ ነውና አትስማው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *