ቆይታ በገሃነም

ተመልሰው ላይከፈቱ የተዘጉ የሚመስሉ አይኖቼን በቀስታ ገለጥኳቸው፡፡ ከፍተኛ ድካም ተሰምቶኛል፡፡ ከወደቅሁበት ተነሳውና ልብሴ ላይ ያለውን አሸዋ በእጆቼ አራገፍኩ፤ ሰውነቴ ድቅቅ ብሏል፡፡ የት ነው ያለሁት? ዙሪያውን ለመቃኘት ድካም የሰበረው አንገቴን አዙሬ አማተርኩ. . .ድንግዝግዝ ያለ ቦታ ነው፤ ፀሃይ አትታይም፣ ጨረቃም የለችም ከዋክብትንም አያውቅም- ሰማዩ፡፡ ሰማዩ ልበለው ሰማያዊ ነገርም የለም ድፍን ጨለማ ነው፡፡ የሚወለካከፉ እግሮቼን ጥቂት እንዳራመድኳቸው አንድ የጥንት ህንፃ ፍርስራሽ የሚመስል ቦታ አየሁ በፍጥነት ተጠጋሁት፡፡ የቆየ ቤተ-መንግስት ቅጥር የሚመስለው መግቢያ ላይ “የገሃነም ደጆች” የሚል ፅሁፍ በመመልከቴ ጉዞዬ ወደ ገሃነም መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡ ጥላሸት የበዛበትን የፈራረሰ ቅጥር አልፌ ስገባ “እንኳን በደህና መጡ” የሚል እና “መልካም ቆይታ” ተብሎ የተፃፈበት የማስታወቂያ ሰሌዳ በማየቴ እየተገረምኩ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡

እንዴት ሞትኩ?

ዕለቱ እሁድ ነበር፤ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ደጆች በሰዎች ትርምስ ተሞልቷል “የዘማሪ ቋሽፍ ኩሼታ ካሴት በ9 ብር” “መርከቢቱ መፅሄት በ5 ብር” በነጋዴዎችና የኔ ቢጤዎች የተጨናነቀውን እግረኛ መንገድ ለመሸሽ ወደ አስፓልቱ ጥግ ገብቼ መጓዝ ጀመርኩ፡፡ ድንገት ከየት መጣ የማይባል ታክሲ በጨረፍታ ሲመታኝ ተንገዳግጄ ቆምኩ፤ ጥያቄ ወደ ውስጤ መጣ ልውደቅ? ወይስ አልውደቅ? ብወድቅ ሹፌሩ ያስገባኝና ሃኪም ቤት ወስዶ በነፃ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ ኤች.አይ.ቪ የመሳስሉትን ያስመረምረኛል አልያም የሆነ ያህል ገንዘብ ትቶልኝ ይሄዳል ስለዚህ ብወድቅ ምንም ጉዳት እንደሌለው በማሰብ ለመውደቅ ጥሩ ቦታ ሳፈላልግ ለካ ታክሲው አልፎኝ ሄዷል፡፡ ተናደድኩ ይሄን ሁሉ አስቤማ በከንቱ አልቀርም አልኩኝና ከላይ የሚመጣው ጥቁር ቮልስ መኪና እንዲገጨኝ ወደ አስፓልቱ ተወረወርኩ፡፡ ግን ቮልሱ ባላሰብኩት ሁኔታ ጎዳኝና ለህልፈተ ሞት በቃሁ፡፡

በመጠን መኖር

በድካም የዛሉ እግሮቼ አሸዋማውን መንገድ እየማሱ ጥቂት እንደተውተረተሩ ከብዙ ጊዜ በፊት ጥሩ ቅርጽ የነበረው ህንፃ ጋር ደረስኩ ወደ ህንፃው እንደተጠጋሁ ከአራት የማያንሱ ሰሌዳዎችን አየሁ በነዚያም ላይ የገሃነም አላማ፣ ራዕይ፣ ተልዕኮ የሰፈረባቸው ሲሆን በአንደኛው ላይ “ወዴት መሄድ ይፈልጋሉ?” የሚል ወሬ ርዕስ ያለው ማስታወቂያ ተመለከትኩ፡፡ “ቢሮ ቁጥር አንድ የሉሲፈር ፀሃፊ” “ቢሮ ቁጥር ሁለት ሉሲፈር” እያለ እስከመዝገብ ያዥ ቁልቁል ወርዷል፡፡ ወደ ሉሲፈር ቢሮ መሄድ እንዳለብኝ ሳስብ አንድ ሰው ከህንፃው ወጥቶ ወደ እኔ መጣና በጨዋ ደንብ እጁን ዘርግቶ “ሉሲፈር” ሲል ስሙን አስተዋወቀኝ፤ ደነገጥኩኝ የሰማሁት ሉሲፈር እና የማየው ሉሲፈር ሁለት የተለያዩ ነገሮች ሆኑብኝ “የዋናው ሉሲፈር የስም ሞክሼ ነህ?” ግራ ቢገባኝ ጠየኩት፡፡ “ኧረ ገሃነም ውስጥ ሞክሼ የለም እኔ ነኝ ዋናው ሉሲፈር እባክህን” በእጆቹ እየመራ ወደ ቢሮው ወሰደኝ፡፡

ቢሮው ፈዘዝ ያለ ቢሆንም ውብ ገፅታ አለው ሉሲፈር ወንበሩ ላይ ከተቀመጠ በኋላ እንድቀመጥ ጋበዘኝ “ውስኪ ቮድካ ምን ይሻልሃል?” ጠየቀኝ ግራ ስጋባ አየኝና እጆቹን እየወዘወዘ ከሳቀ በኋላ “ለካስ ጴንጤ ነህ ሻይ ወይንስ ቡና” ሻይ አዘዝኩኝ፡፡ እሱ ከውስኪው እየተጎነጨ ማውራታችንን ቀጠልን፡፡ “እንግዲህ እኛ የገሃነም ሰዎች እንግዳ ተቀባዮች ነን፡፡ እንዳጋጣሚ ሆነና የመጣህበት ወቅት ብርድ ቢሆንም ጥሩ ቆይታ እንዲኖርህ እመኝልሃለሁ” ብሎ ሲያጨበጭብ ሁለት ቀንድ ያላቸው ጭፍሮች ፈገግ እንዳሉ ሙቀት ያለው ፎጣ ደረቡልኝ፡፡ ከአንዳንድ ቡድኖች ጋር የምቀላቀልበትን መታወቂያ ከሰጠኝ በኋላ መልካም ጊዜ እንደማሳልፍ እምነቱን ገልፆልኝ በሞቀ ፈገግታ ሸኘኝ፡፡

ከዋናው ቢሮ ከወጣሁ በኋላ ወደ ፊት ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ የገሃነም መሃል ከተማ እንደደረስኩ ብዙ ሰዎች ክብ ክብ ሰርተው እሳት ይሞቃሉ፡፡ እንዴት ነው ይሄ ነገር ብዬ አሰብኩ ስንሰበክ እኮ የምንሰማው ገሃነም ውስጥ በእሳት መቃጠል እንዳለ እንጂ በእሳት መሞቅ እንዳለ አልነበረም፡፡ ይሁን ብዬ ጉዞዬን ቀጠልኩ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ታዳጊዎች፣ አዛውንቶች ሁሉም አለ፡፡ አንዳንድ ጭፍሮች ከየቡድኑ ጋር ተቀላቅለው እርስ በእርስ እያወኩ ይስቃሉ- ገሃነም ልዩ ነች፡፡

ወደ አንዱ ቡድን ተጠጋሁ፡፡ ገሃነም ያሉ ሰዎች ሰውን እንግዳ አያደርጉም ከየትም ይምጣ ወይም ቀለሙ ምንም ይሁን ደንታ የላቸውም ብቻ መሳቅን መጫወትን ይወዳሉ፡፡ ጭፍሮች እንኳን ስለ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ማውራትን ተክነውበታል፡፡ አንዱ ጭፍራ ተጠጋኝ ሁለት ቀንድ ጭንቅላቱ ላይ ሲኖረው ጅራቱን ቆልፎ አቀፈኝና “አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?” አለኝ እሽታዬን ስገልፅለት የሁሉም ሰው አትኩሮት ወደ እኔ ሆኖ ነበር፡፡ “በአለም ላይ እድለኛው ወንድ ማን ነው?” አለኝ፡፡ ግራ ተጋባሁ ሁሉም መለፍለፍ ጀመረ፡፡ “አልበርት አን እስታይን” “ ሊዮናርዶ ዳቪንቺ ነው” “አይመስለኝም ጃንሆይ ናቸው” ሁሉም የመሰለውን ተናገረ፡፡ ጭፍራው ጥቂት ዝም ካለ በኋላ “ሚስቱ ከምታጠፋው ገንዘብ የበለጠ ደሞዝ ያለው ወንድ ሁሉ እድለኛ ነው ሀ…ሀ…ሀ” ሁሉም በሳቅ ፈረሰ፡፡

ገሃነም ውስጥ ሁሉ ነገር ለመዝናናት የሚውል ነው፤ ረብሻ የለም፡፡ ገነት በዚህ ሰዐት እንዲህ ታምር ይሆን? ብዬ ራሴን ጠየኩ እንጃ አለኝ ውስጤ ‘አይመስለኝም’፡፡ ድንገት ልቤን ወጋኝ አቃስቼ ወደቅሁ ሁሉም መጯጯህ ጀመረ፡፡ አንድ አምቡላንስ እየከነፈ መጥቶ አፋፍሰው ወደ ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ውስጥ የነበረችው ነርስ ግሉኮስ ሰካችልኝ ግን እድለኛ አልነበርኩም ገሃነም ውስጥ ሞትኩ፡፡

አይኖቼ በቀስታ ተከፈቱ ነጭ ክፍል ውስጥ ነኝ- ሆስፒታል፡፡ ብዙ ሰዎች በዙሪያዬ ይራወጣሉ አጎቴ ከነጫማው ደረቴ ላይ ወጥቶ ይዘላል አየር እንዳገኝ ብሎ፡፡ ብዙ ጉዳት አልደረሰብኝም የተሰካልኝን ጉሉኮስ ነቅዬ ወጣሁ፡፡
እግሮቼ ተገጭቼበት በነበረው አካባቢ ወዳለው ቤተ-ክርስቲያን አመሩ፡፡ አዳራሹ ባዶ ነው፤ እልፍ የተደረደሩ ወንበሮች ከምስባኩ ፊት ለፊት ይታያሉ፡፡ ብቻዬን ጥጉን ይዤ ተቀመጥኩ፡፡

“ለምን እግዚአብሔርን እንከተላለን?” የሚል ጥያቄ አዕምሮዬ ውስጥ መጣ፡፡ እግዚአብሄርን ስለወደድነው የምንከተለው አልመስልህ አለኝ፡፡ ሃጢያት የማንሰራው እየሱስን የምር ስላፈቀርነው እሱን ላለማሳዘን ነው? አይመስለኝም ገሀነምን ስለምንፈራ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የምንከተለው፤ ሃጢያት የማንሰራው አንዳንዴ ቅጣቱን ፈርተን ነው፡፡ ግን ገሃነም እንዲህ ብትሆንስ? ምናልባት ቅንጣት ያህል ምቾት ቢኖረው ኖሮ አብዛኞቻችን የምንከተለው እና የምንታዘዝለትን እግዚአብሔር ጀርባችንን እንሰጠውና ወዲያኛው ፅንፍ እንገኝ ይሆናል. . .ይሆናል. . .

እግዚአብሔርን የመከተል ፊተኛይቱ ትዕዛዝ ይህች ናት
“እስራኤል ሆይ ስማ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፡፡ አንተም በፍፁም ልብህ፣ በፍፁም ነፍስህ፣ በፍፁም ሃሳብህ፣ በፍፁም ሃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” የምትል ናት፡፡

One thought on “ቆይታ በገሃነም”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *