በአለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተወዳጅ የሆኑ ከ100 በላይ መዝሙሮችን በመድረስ እና በማስመለክ የምትታወቀው ዳርሊን ዤክ(Darlene Zschech) መራር ስለነበረው የህይወት ክፍሏ በሰፊው የተረከችበትን መፅሐፍ ለንባብ አበቃች፡፡ The Golden Thread: Experiencing God’s Presence in Every Season of Life (ወርቃማው ልምምድ- የእግዚአብሔርን ሀልዎት በየትኛውም የህይወት ውጣውረድ ውስጥ መለማመድ) የተሰኘ አርዕስት ያልው ይህ መፅሐፍ Wilderness (ምድረበዳ) በሚል ክፍሉ ላይ ዘማሪዋ በልጆችዋ ላይ የተከሰው የ ኦቲስም ህመም እና እሷ ራሷ ለሞት በሚያደርስ የ ካንሰር ህመም ምክንያት ምን ያህል እንደተቸገረች እና ይህንን ወቅት እንዴት በድል እንደተወጣች በሰፊው ተርካበታለች፡፡
Hillsong United (ሂልሶንግ ዩናይትድ) ላይ ከ 25 አመታት በላይ የአምልኮ እና የዝማሬ መሪ የነበረችው ዤክ እንደተናገረችው “የግል ታሪኬን ነው ያካፈልኩት፡፡ ስለቤተሰቤ፣ ስለልጆቼ ነው የፃፍኩት፡፡ ልጆቼ ሲሰቃዩ ያየሁትን ሁሉ ተርኬአለሁ፤ እነሱም አንብበው ፈቅደውልኛል(እንዲታተም)፡፡ እነሱ ያልፈለጉትን አንድም ነገር አላካፈልኩም- እናም ይሄን ክፍል የምድረ በዳው ምዕራፍ ብዬዋለሁ፡፡” ብላለች፡፡
በ 2013 እ.ኤ.አ የተገኘባትን የካንሰር ህመም እና ስቃዩን እያስታወሰች “ሁላችንም የምድረ በዳ ጉዞዎች አሉን” ያለችው ዘማሪዋ “ሁላችንም ያን የክረምት ወቅት እንለማመደዋለን፤ አስፈላጊም ነው፡፡ ክረምት በህይወት መፈራረቅ አውድ ሲታይ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም በ በጋ የማናገኛቸው ልምምዶች በክረምት ብቻ የሚገኙ በመሆናቸው ነው፡፡ የምድረ በዳውን ውበት መፈለግ- የመፅሐፉ ምዕራፍ ስለዚህ የሚያወራ ነው” ብላለች፡፡
ምንም እንኳን ረጅም ጊዜ በፈጀ ህክምና ከ ካንሰር ነፃ መሆኑዋን ብታረጋግጥም ታዋቂዋ የዝማሬ መሪ ያ ወቅት እምነቷን መፈተኑን አልሸሸገችም፡፡ “ሀሌሉያ! ካንሰር ያዘኝ! አላልኩም፡፡ ነገር ግን በዚህ የፈተና ወቅት ስላገኘኋቸው አስደናቂ ነገሮች ሁሌም አመሰግን ነበር” ብላለች፡፡
ዳርሊን ዤክ በአሁኑ ሰዐት ከ25 ዓመታት የተሳካ የአገልግሎት ዘመን በኋላ ከ Hillsong United (ሂልሶንግ ዩናይትድ) በመውጣት ከባለቤቷ ጋር በመሆን Hope Unlimited (ሆፕ አንሊሚትድ) የተባለ ማህበረ ምዕመን መስርተው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ “ ምዕመናን ወደ አለም የተላኩ ቤተክርስቲያን ናቸው እንጂ ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጡ አይደሉም፡፡ “ የምትለው ዤክ በተክርስቲያንን ልክ እንደ ነዳጅ ማዲያ ትመስላታለች፡፡ የቤተክርስቲያን ሚና ሰዎች ነዳጅ ሞልተው እና ተቀጣጥለውእንዲሄዱ እና ለክርስቶስ እንዲኖሩ ማድረግ መሆኑን ተናግራለች፡፡