ቻይናዊው መጋቢ ከመታሰሩ በፊት የፃፈው ደብዳቤ

ከቀናት በፊት 100 ከሚሆኑ የምዕመኑ አባላት ጋር የታሰረው መጋቢ፡ ኮሚኒስት ፓርቲ ምን ያህል ፀያፍ መሆኑን የገለፀበት ደብዳቤ በ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ለንባብ በቅቷል፡፡ መጋቢ ዋንግ ዪ በኮሚኒስተ ፓርቲው ባለስልጣናት ከሚያገለግልበት የሲቹዋን ግዛት በሚገኝ ቤተክርስቲያን ከመታሰሩ ደቂቃዎች ቀደም ብሎ የፃፈው ፅሁፍ የኮሚኒስት ፓርቲ ምን ያህል ጨቋኝ እና ፀያፍ እንደሆነ፤ የእሱ ድርሻ ግን ለስርዐቱ መገዛት ብቻ መሆኑን አትቷል፡፡

በበጎ ፍቃደኞች ተተርጉሞ የተሰራጨው መልዕክት እንደሚያስረዳው “በዚህ የኮሚኒስት ስርዐት ቤተክርስቲያን ምን ያህል እየተገፋች እንደሆነ ሳስብ ውስጤ በቁጣ እና በምሬት ይሞላል፡፡ ሆኖም ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተቋማትን ለመቀየር አልተጠራሁም፤ የክርስቶስን የምስራች ቃል እሰብክ ዘንድ እንጂ” ብሏል፡፡

“ምንም ይሁን ምን ይህ የኮሚኒስት ፓርቲ ከእግዚአብሔር ፍቃድ ስላገኘ ነው የሚገዛን፡፡ የእግዚአብሔርንም ፍቃድ ለመፈፀም ስል ለክርስቶስ ህግ የምገዛ ያክል በደስታ ለህጋቸው እገዛለሁ፡፡ ይህም ሆኖ ግን እንደመጋቢነቴ በቤተክርስቲያን ላይ የሚያደርሱትን ጭቆና ማውገዝ እና በፅኑ መቃወም ይገባኛል፡፡” የሚል መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የመጋቢው እናት እንደሚናገሩት መጋቢው ከሚስቱ ጋር በመንግስት ሀይል በመያዛቸው የ11 ዓመት ልጃቸው በጭንቀት ሳቢያ ለሁለት ቀናት አለመተኛቱን ተናግረዋል፡፡ የመጋቢው እናት ወ/ሮ ቼን እንደሚሉት “(ፖሊሶቹ) በሄድንበት ሁሉ ይከታተሉናል፤ይሰልሉናል ከዚህም የተነሳ የልጅ ልጄ በፍርሀት እና ጭንቀት ውስጥ ይገኛል” ብለዋል፡፡

መጋቢው ረጅም በሆነው ደብዳቤው “በኮሚኒስት ፓርቲው ቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰው በደል መቼ ይቆማል የሚለው ጥያቄ አያሳስበኝም፡፡ አሁም ሆነ ወደፊት ኮሚኒስትም ሆነ ነፃ መንግስት ለእግዚአብሔር ብቻ የተፈቀደውን ህሊና ለመቆጣጠር እስከፈለገ እና ቤተክርስቲያንን ማሳደድ እስካላቆመ ሰላማዊ ተቃውሞዬን አላቋርጥም፡፡ በንግግርም ሆነ በድርጊት የሚገለጥ፤ እግዚአብሔር የሰጠኝ ተልዕኮም የሰብዐዊነት እና የማህበረሰብ ተስፋ በክርስቶስ የሚገኝ ቤዛነት እና በሉአላዊ እግዚአብሔር የሚገኝ ልእለተፈጥሮአዊ ፀጋ ነው፡፡ ይህንንም ለሁሉም ቻይናዊ ማሳወቅ ስራዬ ነው፡፡” ብሏል፡፡

One thought on “ቻይናዊው መጋቢ ከመታሰሩ በፊት የፃፈው ደብዳቤ”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *