ዝለት

(ዝለት)

በወንጌል አ.

መሻት እና ምኞት በሰው ልጅ ህይወት ታሪክ በሙሉ ረግተው አያውቁም፤ ዘወትር ሞገደኞች ናቸው፡፡ ሀይላቸውም
ያን ያህል ነው-እጅግ ተራ የሚባል መሻታችን ነፍሳችንን እንዳልተገራ ፈረስ፤ መንፈሳችንን መልህቅ እንደሌለው
መርከብ ወዲያና ወዲህ ሊንጠው ይችላል፡፡ ከየት እንደመነጨ የማናውቀው ምኞት ቅጽበታዊ በሚመስል ፍጥነት
መላ ሰውነታችንን ወርሶት እናገኘዋለን- ሰው ደካማ ፍጥረት ነው፡፡

በመጠን መኖር–እስካላንቀላፋን ድረስ

ይቺ ህይወት የሚሏት ለአፍታ የምትቆይ ብርሃን ዘላቂ ወጋገኑ መስላው የሚኳትነው ብዙ ነው፡፡ ለአጭር ቆይታዋ
የማይመጥን እቅድ፤ ለከሳሚነቷ የማይገባ ትጋት ተሸክሞ ቀን ከሌት ይለፋል፡ አዎን ሊሳካልን ይችላል! ሊያውም በጥቂት አመታት ጥረት ዋና እና የሁሉም የሚባሉ ህልሞችን ማሳካት ይቻላል፡፡ ኑሮን ማቅናት፣ሀብትን ማፍራት፣ጥሪት መሰብሰብ-በመጨረሻም ባለጠጋ መሆን!

ግን ስጋችን እርካታን ከሚያመነጭበት ፍጥነት አዕላፍ እጥፍ በሆነ መልኩ አዳዲስ ምኞቶች እና ፍላጎቶችን ማምረት
ይቀለዋል፡፡ እናም ትልሞችን ልናሳካ ብንችልም ነፍሳችንን በባለጠጋነት ልናረካት አይቻለንም፡፡ ይልቁንም
ብልጥግናችን ባየለ ቁጥር እርካታችን እየከሰመና እየዛልን እንሄዳለን፡፡ ያረፍን ሲመስለን ከመቼውም በላይ
ቅብዝብዝ ሆነን እንገኛለን፡፡ በመጨረሻም የእርካታንም ሆነ የህይወትን ቁልቁለት እንወርዳለን-ህይወት፣ ብልጥግና
እና ምኞቱ በሙሉ ፀሐይ ይጠልቅባቸዋል፡፡

የያዕ መልዕክት 1፡-11 “ፀሐይ ከትኩሳት ጋር ይወጣልና÷ሳርንም ያጠወልጋልና÷አበባውም ይረግፋልና÷የመልኩም
ውበት ይጠፋልና÷እንዲሁ ደግሞ ባለጠጋው በመንገዱ ይዝላል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *