በመጠን መኖር–እስካላንቀላፋን ድረስ

#ክፍልሁለት

📌ከመጣጥፉ ጋር ሊነበብ የሚገባው የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍል 📋1ኛ ተሰሎንቄ 5:1-9

አንደኛው በመጠን የመኖር ልኬት አለማንቀላፋት ነው፡፡ በመጠን የሚኖር ክርስቲያን አያንቀላፋም። ይልቁንም ዘወትር በንቃት የተስፋውን መገለጥ ይጠባበቃል እንጂ። በክርስቶስ ያመንን አማኞች የማናንቀላፋው ህይወታችን ሁሌም በብርሀን የተሞላ በመሆኑ ነው። የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉ፤ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉ፡፡ በጨለማ ሁለት አይነት ነገሮች ይከወናሉ፡፡ አንደኛው እንቅልፍ(ምቾት፣ እረፍትን ፍለጋ) ሲሆን ሌላኛው እኩይ ምግባር ነው(ስርቆት፣ስካር፣ ዝሙት)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በቀን ደግሞ ሁለት ክዋኔዎች ሲኖሩ አንደኛው በንቃት እና በትጋት ስራን መስራት ሲሆን ሁለተኛው ብርሀን ሁሉን የሚገልጥ ስለሆነ ሰናይ ምግባሮችን መከወን ነው፡፡

ክርስቲያን ወንዶች ሊጠቀሙበት የሚገባ ታዋቂው “የ ቢሊ ግራም መርህ”

የአንድን እውነተኛ ክርስቲያን ህይወት “በቀን መመላለስ” እና “በብርሀን መመላለስ” የሚለው ይገልፀዋል፡፡ ዳግም ተመልሶ ወደዘላለም ቤታችን የሚወስደን ክርስቶስ መቼ እንዲገለጥ ስለማናውቅ ሁሌም በንቃት እንጠብቃለን። ቅዱስ ቃሉ የጌታ ቀን ሌባ በሌሊት እንዲመጣ እንዲሁ ይሆናል ሲል ጌታ እንደሌባ አድብቶ ፤ ክፉ ስለሆነ ውድቀታችንን ጠብቆ ይመጣል ለማለት ሳይሆን አለም በድሎት እና በምቾት ውስጥ ነኝ በምትልበት ሰዐት እንደሚመጣ ለማሳወቅ ነው፡፡ አለም ዕለት ተዕለት ደህነነት እና ምቾት እየተሰማት እንጂ ስጋት ላይ እየወደቀች አትሄድም፡፡ የሰው ልጅ እንደ “የመጨረሻው ዘመን” ምልክት የቀረቡለትን ክስተቶች ዕለት በዕለት ለመፍታት እየታተረ ፤ ዘወትር በማይገታ እና በሚያድግ የፈጠራ ክህሎቱ አለምን የተሻለች ለማድረግ ይጥራል። በዚህ ጥረቱም ከትናንት ይልቅ ዛሬ ላይ ተመችቶት የተደላደለ መስሏል። ከተፈጥሮም ሆነ ከራሱ የሚደርሰውን የማንቂያ ደውል እንዳይሰማ ከዚያ የሚልቅ የድሎት እና “የሰላም ነው” ሙዚቃ ታምቡሩ እስኪቀደድ ይሰማል፡፡ በመሆኑም ዕለት ከዕለት የአለም እንቅልፍ እየከበደ፤ ክርስቶስን መዘንጋቷ እና በራስ መታበይዋ እየጨመረ ስለሚሄድ የክርስቶስ መምጣት ድንገቴ ይሆንባታል።

እኛ ግን የቀን ልጆች፤ የብርሀን ልጆች ነን፡፡ ስለዚህ በየዕለት ኑሮአችን ከአለማውያንም ሆነ ከአማንያን ጋር በሚኖረን ግንኙነት የእምነትን እና የፍቅርን ጥሩር፤ የመዳንን ተስፋ የራስ ቁር እየለበስን በንቃት እና በመጠን እንኖራለን፡፡ የእምነትን አልያም የፍቅርን ጥሩር ባወለቅን ቅፅበት፤ የመዳንንም ተስፋ በጣልን ሰዐት በመጠን መኖራችን ያበቃል፡፡ መራር እና ጥልቅ መንፈሳዊ እንቅልፍ ውስጥ እንገባለን፡፡

🤔እርስዎስ በመጠን ስለመኖር እና በንቃት ተስፋን ስለመጠበቅ ምን ሀሳብ አሎት? እባክዎ በአስተያየት መስጫው ላይ ያጋሩን!
#ክፍልሶስት ይቀጥላል።

2 thoughts on “በመጠን መኖር–እስካላንቀላፋን ድረስ”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *