ሌላው አንጻር

“የቄሳርን ለቄሳር፤የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” የሚለው ተረስቶ ቄሳር እና እግዚሀር የጋራ ንዋይ ባፈሩበት በዚህ ዘመን- ሀይማኖት እና ንግድ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች፤የፍቅር ትምህርት እና የራስ ወዳድነት ግብር ባልንጀሮች ቢሆኑ አይደንቅም፡፡ ከሁለት ሺህ አመታት በፊት በጅራፍ እየገረፈ ያስወጣቸው ነጋዴዎች ረጅም አመት በፈጀ የትጥቅ ትግል መሲሁን ከእሱ በባሰ ጅራፍ ገርፈው ከቤቱ ‘አባረውታል’፡፡

ቤተኛ ከሆነኩበት የክርስትና አስተምህሮ አንስቶ በየትኛውም እምነት የሚያስደንቀኝ ነገር እምነቱ የሚጠይቀው ስብዕና እና አማኙ የሚፈጸመው ግብር እጅግ መራራቁ ነው፡፡ ለቀናት ይህን አስብ ነበር-ፍቅርን እና መሸነፍን፣ሰላም ወዳድነትን እና አንድነትን በዋናነትም ኑሮዬ ይበቃኛልን የሚያስተምር ቅዱስ መጽሀፍ ይዘን ጥላቻን እና ክርክርን፤ ራስ ወዳድነትን እና ስግብግብነትን ማን ይሆን ያስተማረን?

እዩት፤ እሱም አብሮኝ ያለቅሳል፡፡

በርግጥ ብዙዎቻችን “ግራህን ለሚመታህ ቀኝህን መርቅለት” የሚለውን ስናስብ መሆን የፈለግነው ዱለኛውን ይመስለኛል፡፡ “መጎናጸፊያህን ለሚሻ እጀ-ጠባብህንም ተውለት” በሚለው መለኮታዊ ምክር ውስጥ ብዙዎች እጀ-ጠባብ ሰጪውን ሳይሆን ቀሚውን መሆን ስለሚመኙ ቤተ እምነት ለብዙዎች ጭስ አልባ ኢንደስትሪ ሆናለች፡፡

አሁን ግልጽ የሆነው በምክር ቃሉ ውስጥ መውሰድ ከነበረብን የብርሀንነት ሚና በአንጻሩ የቆመውን ጽልመት መርጠናል፤ከታቀደልን የጨውነት ግብር አልጫነት ይታይብናል፡፡ ዘወትር ተገፊ፣ተሸናፊ እና አለም የማይገባው መስለን ልንራመድ ብንጠራም- ገፊ፣አሸናፊ እና ተስፋፊ ሆነን ከትመናል፡፡እንዲያው ግልጽ በማይመስል መንገድ የአለም መግነጢሳዊ ስበት ከቶውን ሳናስበው ስጋችንን ወደመሃሉ እየሳበው ይሆን?

One thought on “ሌላው አንጻር”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *